News News

Back

ወርሃዊ ዜና መፅሄት መጋቢት 2014 ዓ.ም

 

  

        በመንግስት ግዥ አገልግሎት 

           ወርሃዊ ዜና መፅሄት

 

 

በኮሙኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ  

                                                       

 

 

 

መጋቢት 2014 ዓ.ም

     

 

 

ለአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞች በተቋማዊ ባህል ምንነትና ግንባታ ዙሪያ በሁለት ዙር ስልጠና ተሰጠ፡፡

ለአገልግሎቱ አመራሮች እና ሠራተኞች በተቋማዊ ባህል ምንነት እና ግንባታ ላይ በአዳማ ከተማ ከየካቲት 24-26 ቀን 2014 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር እንዲሁም ከመጋቢት 8-10 ቀን 2014 ዓ.ም የሁለተኛው ዙር ስልጠና ተሰጠ፡፡ ስልጠናውን የከፈቱት በአገልግሎቱ የመንግስት ንብረት አስተዳደር/ገበያ ጥናት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር  አቶ ኢቲሳ ደሜ ሲሆኑ የስልጠናው ዋና ዓላማም ሠራተኞች ተቋማዊ የሥራ ባህላቸውን በማዳበር ለተገልጋይ ተገቢውን ክብር እንዲሰጡና የሰራተኛውን ማህበራዊ እሴትም ለማዳበር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡  በስልጠናውም ስለ ተቋማዊ ባህል ምንነት፣አስፈላጊነት፣በተቋማዊ ባህል ግንባታ ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮች፣የተቋማዊ ባህል አይነቶች፣መሰረታዊ ባህላዊ እሴቶች፣ የጥሩ ተቋማዊ ባህል መገለጫዎች እና የጠንካራና ደካማ ተቋማዊ  ባህል ምሳሌዎች በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በኦሮሚያ ፕሬዘዳንት ቢሮ የምርምርና የኢኮኖሚ ዘርፍ ልዩ አማካሪ በዶ/ር ያሬድ ተሾመ ሰፊ ማብራሪያ እና ገለፃ ተደርጓል፡፡ በመቀጠል የቡድን ስራ የተሰጠ ሲሆን በቡድን በመከፋፈል የሚቀጠሉ፣የሚወገዱና የሚጨመሩ ተቋማዊ ባህሎች ላይ ውይይት በማድረግ ከየቡድኑ የተወከሉ አባላት ፕረዘንት አድርገዋል፡፡ ስለሆነም ከፕሬዘንቴሽኑ በመነሳት አሰልጣኙ በመንግስት ግዥ አገልግሎት የሚቀጥሉ፣ የሚወገዱ እና የሚጨመሩ ተቋማዊ እሴቶችን በመለየት አመራሩ ከሰራተኛው ጋር ውይይት እንዲያደርግባቸው በመጋበዝ ስልጠናውን አጠናቋል፡፡

 

በመቀጠል የሰው ሀብት አስተዳደር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ስለሽ በቡድኑ በተደረገው ውይይት ወቅት በአገልግሎታችን መቀጠል፣ መወገድ እና መጨመር አለባቸው ተብለው የተቀመጡትን ተቋማዊ እሴቶች ሁላችንም በደንብ ማየት እንዳለብን ገልፀዋል፡፡ ከሰራተኞች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በየደረጃው ያሉ አመራሮች አድማጭ መሆን እንደሚገባቸውና ከሰራተኛ ጋር የሚደረጉ የውይይት መድረኮች ቢዘጋጁ፣ ስራ ተኮር የሆኑ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ቢሰጡ፣ ለፈጻሚ ስራዎች ተቆጥረው የሚሰጡበትና ክትትል የሚደረግበት ሥርዓት ቢዘረጋ፣ የማያሰሩ አዋጆችና መመሪያዎች ተፈትሸው ቢስተካከሉ፣የቢሮ አደረጃጀትን በሚመለከት ተገልጋይ እየተማረረ ስለሆነ ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ የሥራ ክፍሎች ሰብሰብ ብለው ቢደራጁ፣ የቡድን ስራ በአገልግሎቱ በትክክል አለወይ? የቡድን ስራ ካለ ጠባቂነት ለምን ይኖራል? በአገልግሎቱ የሶሻል ኮሚቴ ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ፣ የማኔጅመንት አባላቱ ጠንካራና ለሠራተኛው አርዓያ መሆን እንደሚገባቸው፣ አገልግሎት አሰጣጣችን ለምንድነው ፈጣን ያልሆነው? ሠራተኛው እርካታ የማያገኝበት ምክንያት የሚሰራው ሥራና የሚያገኘው ጥቅማጥቅም የማይጣጣም በመሆኑ ነው የሚሉ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የህንጻ እድሳት ጉዳይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የሚፈታ እንደሆነ፣ ስራን ቆጥሮ መስጠትና መቀበል ይገባል ለተባለው ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ፣ ደመወዝ ጭማሪ በአገር አቀፍ እንጅ በአገልግሎት ደረጃ እንደማይፈታ፣ ዳይሬክቶሬቶች በመተጋገዝና በመተባበር ስሜት ስራዎችን ማከናውን እንዳለባቸው፣ ሶሻል ኮሚቴ ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ በሁለቱም ዙር አመቻች በመምረጥ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ተገልጿል፡፡

 

በመጨረሻም አቶ ኢቲሳ ደሜ በአገልግሎቱ የመንግስት ንብረት አስተዳደር/ገበያ ጥናት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ሁሉም ሰው የተሰጠውን ኃላፊነት በእኔነትና በባለቤትነት ስሜት በመወጣት የተገልጋይን ምልልስ ለማስወገድ መተጋገዝ እና መረዳዳትን ባህላችን አድርገን መስራት እንደሚገባ በመግለጽ ውይይቱን አጠናቀዋል።

በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር አፈጻጸም እና በሒሳብ አመዘጋገብ  ላይ በአዳማ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡

የመንግስት ግዥ አገልግሎት አመራርና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር አፈጻጸም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር የተበታተነ ፣ቅንጅት የጎደለው፣የህግ ማዕቀፍ ያለመኖር፣የክፍያን ስርዓት ያልተከተለ፣ የመንግስት የሒሳብ አዘገጃጀት እጅግ ወደ ኋላ የቀረ እና የኦዲት እንቅስቃሴ ደካማ የመሆን ችግሮችን ለመፍታት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ 17 አዳዲስ መመሪያዎች ወጥተው በስራ ላይ ውሏል፡፡ የወጡ አዋጆች፣ደንቦች እና መመሪያዎች በባለሙያው አለመታወቃቸው፣ ህግን አውቆና አክብሮ አለመስራት፣የባለሙያ ፍልሰቶች፣ ከሶስተኛ ወገን የሚጠበቁና የሚተገበሩ ስራዎች መዘግየት በአፈጻጸም ወቅት እያጋጠሙ ያሉ ችገሮች መሆናቸውን  አቶ ሙሉቀን አሰግድ በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ወጭ አስተዳዳር ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በስልጠናው ላይ ገልጸዋል፡፡ ባለሙያዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ ለመስራት የወጡ አዋጆች፣ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ግንዛቤ መጨበጥ አለባቸው ብለዋል፡፡

 

በሌላ በኩል በሒሳብ አመዘጋገብ ላይ ገለጻ ያደረጉት የውል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታሁን  የአሸናፊነት ደብዳቤ መሰጠት ውል ተያዘ ማለት አለመሆኑን፣ የሚደረጉ የውል ስምምነቶች ውል ፈራሚው ውሉን ለመፈረም ስልጣን ያለው መሆኑን ፣ውሉን ለመፈረም አቅም እና ፍቃደኝነቱን በአግባቡ መስጠቱን፣ህጋዊ መሆኑን እና ውሉ በጽሁፍ መሆን እንዳለበት እና ገዥው ወጭ አድርጎ መክፍል የሚስችል ገንዘብ (በጀት) መኖሩን መረጋገጥ እንዳለበት በገለፃው አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም በጀት ስራን ለማስፈጸም የሚያዝ ገንዘብ ሲሆን በመንግስት የሚያዙ ሂሳቦች አብዛኛው የአጭር ጊዜ እንደሆኑ እና ኮንትራት በጀት  አንድን ውል ለማስፈጸም የሚያዝ ገንዘብ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም ኤልሲ ሲከፈት የሚመዘገብበት የበጀት  አርእስት እና የዕቃ አጠቃላይ ዋጋ የሚባለው ምን እንደሆነ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

 

   በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር አፈጻጸም እና በሒሳብ አመዘጋገብ ላይ ስልጠና ሲሰጥ

      በሌተርኦፍ ክሬዲት (LC) ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ለመንግስት ግዥ አገልግሎት ለውል አስተዳደር፣ለበጀት እና ፋይናንስ ሠራተኞች በሌተርኦፍ ክሬዲት (LC) ዙሪያ የ3 ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአዳማ ከተማ ተሰጠ፡፡ በስልጠናውም አለም አቀፍ ግዥዎች ሲከናወኑ ገዥና አቅራቢ የሚግባቡባቸው ዓለም አቀፍ የንግድ ስምምነቶች (Incoterms) አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግዥዎችን ስትፈጽም በFOB መሆን እንዳለበት መመሪያ ያመለክታል፡፡ በዓለም አቀፍ ግዥ በFOB  ሲፈፀም አቅራቢው ዕቃዎችን እስከ ወደብ/ ኤርፖርት  ድረስ የማድረስ ኃላፊነት ሰኖርበት ገዥ ከወደብ/ኤርፖርት ወጪውን እና ኃላፊነት ይረከባል፡፡ የክፍያ ስርዓቱ በኤልሲ የሚፈጸም ሲሆን ገዥ የሚኖርበት ሀገር ባንክ በስምምነታቸው መሰረት ሰነድ ሲደርሰው ክፍያው ለአቅራቢው እንዲከፍል ለአቅራቢው ሀገር ባንክ ያሳውቃል፡፡

 

ሌተርፍ ክሬዲት (LC) የክፍያ ስርዓት ጊዜ ከአቅራቢው የሚላኩ ሰነዶችን በማየት የተጫነውን ዕቃ ጥራት ማረጋገጥ እንዴት እንችላለን በሚል ከስልጠና ተሳታፊዎች ለተነሳው ጥያቄ የውል አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታሁን ዓለም አቀፍ አሰራር በኤልሲ ክፍያ ስርዓት ዕቃዎችን ሳንረከብ ክፍያ ይፈጸማል ማለት አይደለም ገዥው አቅራቢ ወደብ/ኤርፖርት ላይ የዕቃዎችን ጥራት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን በእኛ ሀገር አቅራቢ ወደብ ሄዶ የማረጋገጥ ክፍተት አለ እንደዚህ ያለ ልምድ የለንም በተቻለ መጠን መሰረታዊ ሰነድ የሚባሉትን የጭነት መረጃዎች፣የምን ሀገር ስሪት እንደሆነ፣የአቅራቢው ሀገር  ምክርቤት ያረጋገጠው መሆኑን፤አግባብነት ያለው የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እና የፓኬጅ ዝርዝር ይታያሉ በማለት አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ግዥዎችን ቦታው ድረስ በመሄድ ፈትሸው መቀበል እንደሚኖርባቸው በፌዴራል አቃቤ ህግ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የቅድመ ክፍያ እና የኤልሲ የሒሳብ አርዕስት አንድ መሆን የኦዲት ግኝት እየሆነ ተቸግረናል ተባለ፡፡

በመንግስት ግዥ አገልግሎት ከመጋቢት 1 እስከ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ለፋይናንስ እና ውል አስተዳደር ባለሙያዎች ባዘጋጀው የስልጠና መድረክ የቅድመ ክፍያ እና ኤልሲ ሒሳብ በአንድ አርዕስት የሚመዘገብ መሆኑ በቅድመ ክፍያ መመሪያ መሰረት  በ7ቀን ውስጥ አልተወራረደም በማለት የኦዲት ግኝት እየተባሉ መሆኑን፣ መስሪያ ቤቶች ለተፈጸመላቸው ግዥ ከአገልግሎቱ ከዲ አካውንት ከበጀታቸው በላይ ቢከፍላቸውም ቀሪውን ገንዘብ ለመክፈል ፍቃደኛ አለመሆን፣ ከተጠቃሚ መስሪያ ቤቶች ለተለያዩ ግዥ በአገልግሎቱ በዲ አካውንት ገቢ የሚደረግ ገንዘብ ተለይቶ አለመታወቁ፤ለየትኛው መስሪያቤት ከዲ አካውንት እንደተከፈለ የሚሳይ የተደራጀ መረጃ አለመኖር እንደ አገልግሎቱ ያጋጠሙ ችገሮች መሆናቸውን ከስልጠናው ተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን በዚህ ምክንያት የተንጠልጣይና ተከፋይ ሂሳቦችን ለማወራረድ እየተቸገሩ መሆኑን ከግዥና ፋይናንስ ዳይሬክተሬት የተሳተፉ ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡

የኤልሲ ክፍያ ከቅድመ ክፍያ የተለየ መሆኑን ለኦዲተሮች የማስገንዘብ እና በቀጣይነት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሄ ላይ መሰራት እንዳለበት እና የአገልግሎቱ የተንጠልጣይና ተከፋይ  ሂሳቦችን አለመወራረድ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ እና ከተጠቃሚ  መስሪያቤቶች በአገልግሎቱ ዲ አካውንት ገቢ የሚደረጉ ገንዘቦች በዝርዝር ተመዝግበው መያዝ እንደሚኖርባቸው እና ያጋጠሙ ችግሮቸን ለመፍታት የአሰራር ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ተብሏል፡፡

 

ለአገልግሎቱ ወጣት ሰራተኞች በስብዕና እና ግብረገብነት እንዲሁም በወጣቶች ፖሊሲ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

በአገልግሎቱ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ለአገልግሎቱ ወጣት ሠራተኞች በስብዕና እና ግብረገብነት እንዲሁም በወጣቶች ፖሊሲ ዙሪያ ከመጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ ከተማ የሶስት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ። ስልጠናውን የከፈቱት በአገልግሎቱ የዋና ዳይሬክተር ተወካይ ወ/ሮ አበባ አለማየሁ ሲሆኑ የስልጠናው ዋና ዓላማም በሀገራችን መንግስት ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ፣በሀገር ግንባታ ሂደት ሰፊ ንቁና የተደራጀ ተሳትፎ ያለውና ተጠቃሚ የሆነ፣የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ተረክቦ የሚያስቀጥል ወጣት ትውልድ ለመፍጠር የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ፓኬጆችና ስትራቴጅዎችን በመቅረጽ በወጣቶች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሰው የአገልግሎታችን ወጣት ሠራተኞችም ተሳትፏቸውን የሚያረጋግጡበት መድረክ በመፍጠር በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ ለማበረታታት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከአገልግሎታችን ሠራተኞች 90 ፐርሰንቱ ወጣት መሆናቸው ለአገልግሎቱ ተልዕኮ መሳካት ትልቅ ስንቅና ተስፋ የሚጣልበት እንደሆነም ወ/ሮ አበባ አመላክተዋል፡፡ 

 

               ለአገልግሎቱ ወጣት ሠራተኞች በስብዕና እና ግብረገብነት እንዲሁም

               በወጣቶች ፖሊሲ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሲሰጥ

በስልጠናውም በስብዕና እና ግብረገብነት ምንነት፣ የግብረገብነት (ሞራል) እድገት፣ አፍራሽ ባህሪያት፣ ግብረገብነት (ሞራል) ለምን ይዳከማል እና የግብረገብነት (ሞራል) እድገት እንዳይዳከም መፍትሄው ምንድነው፣ ከዜጎችስ ምን ይጠበቃል? እንዲሁም በወጣቶች ፖሊሲ ዙሪያ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጡ የስልጠና ባለሙያዎች ሰፊ ማብራሪያ እና ገለፃ ተደርጓል፡፡ በመቀጠልም ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን    በሀገራችን ያለውን የስራ አጥነት ችግር መቅረፍ እና የትምህርት ጥራት ላይ መንግስት ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት፣የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ምን ያህል እየሰራ ነው? መንግስት ፖሊሲ መቅረጽ ብቻ ሳይሆን አፈፃፀሙን በሚገባ መገምገም እንዳለበት፣ወጣቶች በነፃ እንዲደራጁ እና ሐሳባቸውን በዲሞክራሲዊ አካሄድ እንዲገልጹ መበረታታት አለባቸው የሚሉ ዋና ዋና ጥያቄዎች ተነስተው ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

 

በመጨረሻም በአገልግሎቱ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ እታለማሁ ጥላሁን የአገልግሎቱ ወጣት ሠራተኞች በመልካም ስነ ምግባር ታንፀው በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል በቀጣይም ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ በመግለፅ ስልጠናውን አጠናቀዋል፡፡  

አገልግሎቱ ለወልዲያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎቱ የሚውል የውሃ ማመላለሻ ቦቲ ግዥ ለመፈጸም ያወጣውን ውስን ጨረታ የቴክኒክ ሰነድ ከፈተ፡፡   

የመንግስት ግዥ አገልግሎት ለወልድያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት የሚውል 1400-1600 ሊትር የሚይዝ  የውሃ ማመላለሻ ቦቲ ግዥ ለመፈጸም  በጨረታ ቁጥር PPS/WU/NRB/PG/179/06/2014  የወጣውን ብሔራዊ ውስን ጨረታ የቴክኒክ ሰነድ መጋቢት 19 ቀን 2014 . ከጠዋቱ 415 ላይ  በአገልግሎቱ ትንሹ የመሰብሰቢያ አዳራሽ  ተከፈተ፡፡ በጨረታው ስምንት ድርጅቶች የተጋበዙ ቢሆንም የጨረታ ሰነድ ያስገባ ድርጅት አንድ መሆኑን ከመንግስት ግዥ ዳይሬክቶሬት በተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡