News News

Back

የየካቲት ወር ወርኃዊ ዜና መፅሔት

በመንግስት ግዥ አገልግሎት 

 ወርኃዊ ዜና መፅሔት

 

በኮሙኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ  

 

 

የካቲት 2014 ዓ.ም

     

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  በአገልግሎቱ የሥራ ላይ ግምገማና የመስክ ምልከታ አካሄደ፡፡  

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለመስሪያ ቤታችን ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም በመ/ቤታችን በአካል በመገኘት የሥራ ላይ ግምገማና የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት የአገልግሎቱን አፈፃፀም ለመገምገም እንዲያመች የአገልግሎቱ የ6 ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ በወ/ሮ አበባ አለማየሁ ለቋሚ ኮሚቴው ገለፃ ተደርጓል፡፡ በመቀጠልም ቋሚ ኮሚቴውም የአገልግሎቱን የቢሮ አደረጃጀት፣ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም፣ የንብረት አያያዝ፣ አጠባበቅና አወጋገድ ሂደትን በተመለከተ ምልከታ አድርጓል፡፡

 

ኮሚቴው የቀረበለትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በጥንካሬና በድክመት ያያቸውን ነገሮች ለማኔጅመንቱ ገለፃ አድርጓል፡፡ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች የግዥ ዕቅዳቸውን በወቅቱ ሳያቀርቡ ሲቀሩ የሚያቀርቡበት አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ የለም ወይ? አገልግሎቱ ግዥ ከመፈፀምና ንብረት ከማስወገድ ስራዎች በተጨማሪ ተቋማት ወደ ዘመናዊ የግዥ ሥርዓት እንዲገቡ የማማከር ስራ ቢሰራ፣ ከተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች ጋር ተያይዞ በአግባቡ በማጣራት ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባ፣ ሴቶች ማብቃት እንዲሁም ከስርዓተ ፆታ አካታችነት ስራዎችን በሚመለከት ክፍሉ መደራጀትና ሥራው በአግባቡ መሰራት እንዳለበት፣ለአገልግሎቱ በአዋጅ የተሰጡ ስራዎች ለምሳሌ የስንዴና የተሽከርካሪ ግዥዎች፣ እንዲሁም የሚወገዱ ተሽከርካሪዎችን ሌሎች ተቋማት ስራውን እንዲሰሩት የሚደረገው ትክክል እንዳልሆነና አገልግሎቱ ተግባርና ኃላፊነቱን አውቆ በደንብ መስራት እንዳለበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተለይ በአቅርቦት ላይ ትልቅ ችግር እያጋጠመ እንደሆነና ችግሩን ለመፍታት አገልግሎቱ ተጠናክሮ መስራት እንዳለበት፣የሚገዙ ዕቃዎች ጥራት በተጠቃሚ መ/ቤቶች ዘንድ እንደችግር እየተነሳ ስለሆነ አገልግሎቱ ከተስማሚነት ምዘና ድርጅት ጋር ተቀናጅቶ ስራውን ቢሰራ፣ አገልግሎቱ ያለ ኃላፊ ከሰባት ወር በላይ ቆይቷል ስለሆነም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ኃላፊ እንዲመደብ ቢደረግ፣ የኬሚካል አወጋገድን በሚመለከት አገልግሎቱ ምን እየሠራ ይገኛል፣የእርካታ ዳሰሳ ጥናት የውስጥ ሠራተኛ ሳይረካ የውጭ ተገልጋይ እንዴት የበለጠ ሊረካ ይችላል እንዴት ተተንትኖ ነው ጥናቱ የተካሄደው ቢብራራ የሚሉ አስተያየትና ጥያቄዎች በቋሚ ኮሚቴው ቀርበዋል፡፡

 

በተጨማሪም የሰራተኞች የጥቅማጥቅም ችግሮች እንዳሉባቸው፣ የሀገር ውስጥ ስልጠናዎች ቢኖሩም ተደጋጋሚነት ያለውና በስራቸው ላይ ለውጥ ሊያመጣ አለመቻሉን፣ከሀገር ውጭ የሚሰጡ ስልጠናዎች አለመመቻቸታቸውን፣ደመወዝ ከስራው ከብደት ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ ለሰራተኞች ፍልሰት ምክንያት መሆኑን፣ ከቢሮ ውጭ ለሚሰሩ ስራዎች በአገልግሎቱ የተሽከርካሪ ችግር መኖሩን ካነጋገሯቸው ሠራተኞች መረዳት መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡

                               

                  ቋሚ ኮሚቴው ከአገልግሎቱ ሰራተኞች ጋር ውይይት ሲያደረግ

በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ ባለው ውስን የሰው ሀይል እንዲሁም ፋሲሊቲ ባልተሟላበት ሁኔታ ስራዎችን ለመስራት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡  የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ወ/ሮ አበባ አለማየሁ፣ የንብረት ዋጋ ግምትና ማስወገድ  ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢቲሳ ደሜ  እንዲሁም የሚመለከታቸው ዳይሬክቶሬቶች በቋሚ ኮሚቴው በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን አጫጭር ስልጠናዎች የሚሰጡበት ምክንያት አገልግሎቱ ባለው የበጀት አቅም መሆኑ፣ የሰራተኛ መልቀቅ ዋናው ምክንያት የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ቋሚ ኮሚቴው ሊያግዘን እንደሚገባ፣ የኬሚካል አወጋገድን በሚመለከት ስራው ለአገልግሎቱ በማቋቋሚያ ደንቡ እንዳልተሰጠው እና ይህን የሚሰራው የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እንደሆነ፣በአገልግሎቱ የተሽከርካሪ እጥረት እንዳለና ችግሩ እንዲፈታ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ ቢያደረግ፣ የእርካታ ዳሰሳ ጥናትን በሚመለከት እንደ አገልግሎት በመካከለኛ ደረጃ ያለ እንደሆነና እንደገና የሚታይበት ሁኔታ እንደሚኖር፣የአገልግሎቱ ስያሜ የመንግስት ግዥ አገልግሎት ቢባልም የማስወገዱን ስራም ተጠናክሮ እንደሚሰራና የሚወገዱ ንብረቶች የገንዘብ ጣሪያ ሰርኩላር በስህተት የተላለፈ በመሆኑ እንደሚስተካከል እና ሌሎች በአገልግሎቱ በእጥረት የተነሱ ጉዳዮች ከሚመለከታቸው መ/ቤቶች ጋር በመስራት እንደሚፈቱ አስረድተዋል፡፡

 

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው የ300 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ተጠናክሮ ግዥው በአገልግሎቱ መፈፀም እንዳለበት፣ የተጠቃሚ መ/ቤቶች ፍላጎት ከማቅረብ ጋር ተያይዞ ችግሩን ለመቅረፍ የአሰራር ስርዓት ቢዘረጋ፣ተከፋይና ተስብሳቢ ሂሳቦች ላይ ችግሩን ለመቅረፍ ተጠናክሮ መሰራት እንዳለበት፣የዕቃ ጥራት ጋር ተያይዞ በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የምርምር ስራ የሚሰራበት ሁኔታ ቢመቻች፣የስርዓተ ጾታና የሴቶችን አደረጃጀት በሚመለከት አገልግሎቱ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ፣ የግዥ አዋጁ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ከሚመለከተው ተቋም ጋር መነጋገር  ተገቢ እንደሆነና በአጠቃላይ በአገልግሎቱ ለስራ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በአፋጣኝ በመፍታት እና የሰራተኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅም የሚስተካከልበትን መንገድ በመፍጠር ላይ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስቧል::  

 

አገልግሎቱ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ዕቃዎችን ለወልድያ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ አደረገ፡፡  

በአገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ጁንታው በከፈተብን መጠነ ሰፊ ጦርነት ምክንያት በርካታ መሠረተ ልማቶች ከጥቅም ዉጪ ከሆኑባቸው ክልሎች በዋናነት ከሚጠቀሱት አማራ እና አፋር ክልሎች መሆናቸው ይታወሳል፡፡

በዚሁ መጠነ ሰፊ ጦርነት ምክንያት ከወደሙት መሠረተ ልማቶች መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች፣ የአስተዳደርና የጤና ተቋማት በጥቂቱ የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል ወልድያ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው፡፡

የአገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእያንዳንዱ ዜጋ ልጆች የሚማሩበት ተቋም እንደመሆኑ መጠን የመንግስት ግዥ አገልግሎት የተለያዩ ግምታዊ ዋጋቸው ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚሆን ያገለገሉ ወንበሮችን፣ ኮምፒውተሮቸን፣ ዩፒኤሶችን፣ የፋይል ካቢኔቶችን እና ሌሎች ንብረቶችን  ዩኒቨርሲቲው ድረስ  በመሄድ ድጋፍ አደርጓል፡፡

 

 

      የአገልግሎቱ አመራሮች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለወልድያ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ሲያደርጉ

  •    መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶችና አቅራቢ ድርጅቶች  ጋር የጋራ የምክክር መድረክ ተካሄደ 

የፌዴራል መንግስት ግዥ አገልግሎት ከፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እና ከማዕቀፍ ግዥ አቅራቢዎች ጋር በአገልግሎቱ የስድስት ወራት የግዥና ንብረት ማስወገድ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡   

የምክክር መድረኩን የከፈቱት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ወ/ሮ አበባ አለማየሁ   ሲሆኑ ግዥን በተበታተነ መልኩ ከመፈፀም ይልቅ በአንድ ማዕከል መፈፀሙ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በመግለጽ አገልግሎቱ ስራ ከጀመረበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የብረት፣ የስንዴ፣የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ የህንጻ ግንባታ፣ ለመማር ማስተማሩ የሚያገልግሉ ማጣቀሻ መጽሃፍት፣ የላብራቶሪ፣የመመገቢያ የተለያዩ ፈርኒቸሮች ዕቃዎች፣እንዲሁም የማዕቀፍ ስምምነት ግዥዎችን በድምሩ ከ105 ቢሊየን ብር በላይ ግዥ መፈጸሙንና ንብረቶችን በማስወገድ ደግሞ ከ850 ሚሊየን ብር በላይ ቢ በማግኘት ለመንግስት ግምጃ ቤት ፈሰስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ 

ያዝነው 2014 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመትም የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች እና የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የሚጠቀሙባቸውን ተመሣሣይ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በ280.9 ሚሊየን ብር ግዥ መፈፀሙን እና በ2013 በጀት ዓመት ተጀምረው ወደ 2014 በጀት ዓመት የተዛወሩ የተለያዩ የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎች ግዥ የግዥ ሂደታቸው ተጠናቆ ከ15 አቅራቢ ድርጅቶች ጋር 24 ዉሎች በ369.8 ሚሊየን ብር ውል ተፈርሞ 187 ባለበጀት መ/ቤቶችና 45 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለና የተለያዩ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ 22.9 ሚሊየን  ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል። 

በምክክር መድረኩ የአገልግሎቱን የስድስት ወር የግዥና የውል አስተዳደር አፈፃፀም ያቀረቡት የአገልግሎቱ የውል አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታሁን ሲሆኑ በግማሽ ዓመቱ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች እና የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የሚጠቀሙባቸውን ተመሣሣይ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በ280.9 ሚሊየን ብር ግዥ መፈጸሙንና በሌላ በኩል በ2013 በጀት ዓመት ተጀምረው ወደ 2014 በጀት ዓመት የተዛወሩ የተለያዩ የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎች ግዥ የግዥ ሂደታቸው ተጠናቆ ከ15 አቅራቢ ድርጅቶች ጋር 24 ውሎች በ369.8 ሚሊየን  ብር ውል ተፈርሞ 187 ባለበጀት መ/ቤቶችና 45 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ፤የ360 ሞተር ሳይክሎችን ግዥ ለመፈጸም የግዥ ሂደታቸው ተጠናቆ በ57.2 ሚሊየን ብር ውል መፈረሙን ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም በግማሽ ዓመቱ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም አሁንም ቢሆን በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ተጠቃሚ መ/ቤቶችም ሆነ በአቅራቢ ድርጅቶች የሚታዩ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ተቋማት የግዥ ዕቅዳቸውን በወቅቱ የማይልኩ መሆናቸው በግዥ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳደሩና እቅዳቸውን በወቅቱ በሚያቀርቡ መ/ቤቶች ላይም ጫና እየፈጠረ መሆኑከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት በመኖሩ ምክንያት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በቶነር እና በጽሕፈት መሣሪያ ዕቃዎች ላይ የአቅርቦት ችግር ያጋጠመ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡ ይሁንና ይህን ችግር ለመቅረፍ አንዳችን በአንዳችን ሳናሳብብ ሁላችንም ተጠቃሚ ለመሆን በመተሳሰብ  በጋራ መስራት አለብን በማለት አጠናቀዋል፡፡

የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሹንቃ አዱኛ አገልግሎቱ በንብረት ማስወገድ በኩል ከሚወገዱ ንብረቶች የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የሚገልፅ ሪፖርት አቅርበዋል። በዚህም መሰረት 2014 በጀት ዓመት ስድስት ወራት  ከተሽከርካሪዎች ፣ከተለያዩ ንብረቶች እና ከቁርጭራጭ ብረታ ብረቶች (scrap) ሽያጭ ከ22.9  ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል በማለት ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን በፌዴራል መ/ቤቶች በሚወገዱ ንብረቶች አያያዝ ላይ ውስንነቶች መኖራቸው፣ ከአንዳንድ መ/ቤቶች እንዲወገዱ የሚላኩ ተሽከርካሪዎች እና ንብረቶችን መረጃ አሟልተው ያለመላክ ዋና ዋናዎቹ  ችግሮች   መሆናቸውን አቶ ሹንቃ ገልፀዋል፡፡

                         የመድረኩ ተሳታፊዎች በከፊል

በመቀጠል ከመድረክ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ተሳታፊዎቹ እንደገለፁት አገልግሎቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እና የሚያበረታታ ቢሆንም ዕቃ አቅርቦት በወቅቱ ተፈፅሞ መስሪያ ቤቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ አገልግሎቱ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት፣ የፎቶ ኮፒ ማሽን ቶነሮች፣ ሶፍት፣ ወረቅትና እስክቢሪቶ አብዛኛውን ጊዜ ጥራታቸውን ያልጠበቁ እንደሆኑ እና የሚቅርቡ ዕቃዎችም በስፔሲፊኬሽኑ መሰረት እንደማይቀርቡ፣ የደንብ ልብስ ግዥን በተመለከተ ተጠቃሚ መ/ቤቶች በፈለጉት አይነትና ጊዜ እያገኙ እንዳልሆነ ስለሆነም አገልግሎቱ በዚህ ዙሪያ  ተጠናክሮ መስራት እንዳለበት፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና የኬሚካል አወጋገድን በተመለከተ አገልግሎቱ ምን ጥረት እያደረገ ይገኛል፣ የተሽከርካሪ ጥገናን በተመለከተ በማዕከል እንዲሆን አገልግሎቱ ምን ያሰበው ነገር አለ፣ ሰነድ አልባ ተሽከርካሪዎች እንዴት መወገድ አለባቸው፣ በዕቃዎች አቅርቦት ዙሪያ የተሻለ ውድድር እንዲኖር የአቅራቢዎች ቁጥር ቢጨመር እና የመሳሰሉት ከፌዴራል መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሲሆኑ፣ 

                       የመድረኩ ተሳታፊዎች በከፊል

አቅራቢዎቹ በበኩላቸው በገቢዎችና ጉምሩክ አሠራር እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የገበያ ዋጋ ባለመረጋጋት በኮንቴነር ዋጋ ጭማሪ ምክንያት  ከውጭ የሚያስመጧቸው ዕቃዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ አብዛኞቹ የፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች ዕቃ በወቅቱ ተረክበው ክፍያውን  በወቅቱ እንደማይከፍሏቸው እና  የዋጋ ማስተካከያ ሳይደረግ አቅርቦት እንደሚፈጽሙ ገልፀዋል፡፡ 

                             አቅራቢዎች አስተያየትና ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ

በመጨረሻም ለተነሱት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከአቅራቢዎችም ከመድረክም መልስ የተሰጠ ሲሆን፣ በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ውስጥ የሌሉትን እቃዎች ተቋማት ግዥውን በራሳቸው እንዲፈፅሙ አገልግሎቱ ቀደም ብሎ በደብዳቤ ያሳወቀ መሆኑ፣ የዕቃዎችን ጥራት በሚመለከት ስፔሲፊኬሽን የሚዘጋጀው በሚመለከታቸው አካላት እንደሆነና ጥራትን አገልግሎቱ የሚያየው Fit for Purpose (ለታቀደለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንጅ ለቅንጦት እንዳልሆነ)፣ አንድ አቅራቢ ለሶስት ዓመታት እንዲያቀርብ ሲደረግ አቅራቢዎችን ሞኖፖሊ ያደረጋል ለተባለው አገልግሎቱ እንደ ችግር እንደማያየውና ከመንግስትም የተሰጠ አቅጣጫ ከመሆኑ በተጨማሪ አገልግሎቱ ግዥ የሚፈፅመው አለም አቀፍ ግልፅ የጨረታ ማስታወቂያ አውጥቶ በመሆኑ ማንኛውም ነጋዴ በጨረታው ተሳትፎ አሸናፊ ከሆነ አቅርቦት መፈጸም እንደሚችል፣  ተጠቃሚ መ/ቤቶች የግዥ ዕቅዳቸውን በወቅቱ ለአገልግሎቱ ስለማያቀርቡ በአቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ እና እቅዳቸውን በወቅቱ ባላቀረቡበት ወቅት ቅሬታ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ፣ የማዕቀፍ ስምምነት ውል ምንድነው ለተባለው አጠቃላይ የውል ስምምነት እንደሆነና ውል የሚባለውም የግዥ ትዕዛዙ በመሆኑ በዚህ መሰረት ግዥው መፈፀሙን ማረጋገጥ እንደሚገባ፣ሰነድ አልባ ተሽከርካሪዎች አወጋገድን በተመለከተ ተሽከርካሪ መዝጋቢዎች ሰነድ አልባ ነው ብለው አረጋግጠው ከላኩ አገልግሎቱ እንደሚያስወግድ፣  የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አወጋገድን በሚመለከት ፈቃድ ላለቸው የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ አስወጋጅ መ/ቤቶች እንዲያስወግዱ ቢደረግ፣ የኬሚካል አወጋገድን በተመለከተ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡  ተቋማት የግዥ ዕቅዳቸውን በወቅቱ ባለማቅረባቸው ምክንያት በእቅድ መሰረት እቃዎችን ለማቅረብ አገልግሎቱ እየተቸገረ በመሆኑ ተቋማት የግዥ ዕቅዳቸውን በወቅቱ እንዲያቀርቡ ማሳሰቢያ የተሰጠ ሲሆን የማዕቀፍ ስምምነት ግዥም ሆነ የንብረት ማስወገድ ስራ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ስላለው ተጠቃሚ መ/ቤቶች፣ አቅራቢ ድርጅቶችም ሆነ ባለድርሻ አካላት ተቀራርበን በመወያየት ችግሩን በጋራ በመፍታት የተሻለ ስራ መስራት ተገቢ እንደሆነ ተገልጾ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

አገልግሎቱ እቅዳቸውን በወቅቱ ላቀረቡ 23 የመንግስት ዩኒቨርሰቲዎች በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ሊፈፅም ነው፡፡  

በአገራችን የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማሩን ስራ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያካሂዱ አገልግሎታችን በርካታ ግዥዎችን  ፈጽሞ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመትም እቅዳቸውን በወቅቱ ላቀረቡ 23 የመንግስት  ዩኒቨርሰቲዎች ከ2014-2016 በጀት ዓመት አገልግሎት የሚውሉ የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎችን የተለያዩ የኢንፎርሜሽን  ቴክኖሎጅ፣ የፕሪንተርና ፎቶ ኮፒ ማሽን ቶነሮችን በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ለመፈፅም ያወጣውን ዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ የቴክኒክ ሰነድ ከፍቶ የቴክኒክ ሰነድ ግምገማ እያካሄደ ይገኛል፡፡  

አገልግሎቱ ለቦረና ዩኒቨርሲቲ አገልግሎቱ የሚውሉ የተለያዩ የተማሪዎች መገልገያ    መሳሪዎችን ግዥ ለመፈፀም የቴክኒክ ሰነድ ግምገማ እያካሄደ ነው፡፡  

የመንግስት ግዥ አገልግሎት ለቦረና ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት የሚውሉ የተማሪዎች መገልገያ ፈርኒቸር እና የተፈጥሮ ሳይንስ የላብራቶሪ ፈርኒቸሮችን፣የሶሻል ሳይንስ የማጣቀሻ መፅሀፍት፣ የተፈጥሮ ሳይንስ የላብራቶሪ መሳሪዎች ግዥ ለመፈፀም ያወጣውን ብሔራዊ ግልፅ ጨረታ የቴክኒክ ሰነድ ከፍቶ የቴክኒክ ሰነድ ግምገማ እያካሄደ ይገኛል፡፡