News News

Back

ወርኃዊ ዜና

 

 

በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት 

በባለፈው እና በሚቀጥለው ወርሃዊ ዜና መፅሄት

 

በኮሙኒኬሽን እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

                                                       

 

 

 

መስከረም 2014 ዓ.ም

 

                 በባለፈው  

በውል  አስተዳደር  ምንነትና ተያያዥ  ፅንሰ  ሃሳቦች፣ በግዥ  አፈፃፀም እና በመንግስት  ግዥ  ሥርዓት  የሙያ  ስነምግባር  ዙሪያ  በአዳማ  ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡

በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ለግዥ እና  ውል አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊዎች እና  ሠራተኞች  በውል  አስተዳደር  ምንነትና ተያያዥ ፅንሰ  ሃሳቦች፣ በግዥ  አፈፃፀም  እና በመንግስት ግዥ  ሥርዓት  የሙያ  ስነምግባር  ዙሪያ በአዳማ ከተማ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጽዋዬ ሙሉነህ ሲሆኑ ስልጠናው በበጀት ዓመቱ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሰጠቱ በተለይ በግዥና በውል አስተዳደር የስራ ክፍል ውስጥ ለሚሰሩ ባሙያዎች በዘርፉ ተገቢው እውቀት ኖራቸው ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚረዳቸው ገልፀዋል፡፡

 

             የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት

 

የውል አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታሁን በውል አስተዳደር  ምንነትና ተያያዥ ፅንሰ  ሃሳቦች ስልጠና የሰጡ ሲሆን ውል አስተዳደር ምንድነው፣ስለውል ክፍሎች፣ የክፍያ ዘዴዎች፣ በውል አስተዳደር አፈፃፀም ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል::

 

 

በውል አስተዳደር ምንነትና ተያያዥ ፅንሰ ሃሳቦች ዙሪያ ስልጠና ሲሰጥ

 

በመቀጠል በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከፍተኛ የግዥ ባለሙያ የሆኑት አቶ መሀመድ አሊ በግዥ አፈጻጸምና በመንግስት ግዥ ስርዓት ሊኖር ስለሚገባ የሙያ ስነምግባር ዙሪያ ስልጠና የሰጡ ሲሆን የስልጠናው ይዘት በዋናነት፡-የመንግስት ግዥ አጠቃላይ ገፅታ፣ በመንግስት ግዥ ላይ ሚና ያላቸው አካላት ተግባርና ኃላፊነት፣የግዥ ኡደት፣የግዥ ዕቅድ፣ የግዥ ዘዴዎች፣መደበኛ የጨረታ ሰነድ ይዘትና አጠቃቀም፣የጨረታ ግምገማ፣ቅሬታና አቤቱታ አቀራረብና ውሳኔ አሰጣጥ በመንግስት ግዥ አፈፃፀም ሊኖር ስለሚገባ የሙያ ስነምግባር በተለይ ከግዥ ባለሙያዎች የሚጠበቅ ስነምግባር ምንድነው? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ገለጻ አድረገዋል:: ስለሆነም በውል አስተዳደርና በግዥ አፈፃፀም ዙሪያ በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከሰልጣኞች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም በአሰልጣኞች ምላሽ ተሰጥቷል::

F

 

 

            በግዥ አፈጻጸምና በመንግስት ግዥ የሙያ ስነምግባር ዙሪያ ስልጠና ሲሰጥ

 

በመጨረሻም የአገልግሎቱ የግዥና ውል አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አበባ አለማየሁ በግዥና ውል አስተዳደር የስራ ክፍል ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች የግዥ አዋጆችንና መመሪያዎችን በሚገባ በማንበብ ስራዎችን በጥንቃቄ፣ ስነምግባር በተላበሰ መልኩ፣ሚስጢራዊነቱን በጠበቀና  በቅንነት ለማከናወን ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው ማሳሰቢያ  በመስጠት  ውይይቱን አጠናቀዋል:: 

 

በሽያጭ የሚወገዱ ያገለገሉ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች እና ንብረቶች የግምገማ ውጤት ለአሸናፊዎች ይፋ ተደረገ፡፡  

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ያገለገሉ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችን እና ንብረቶችን በሽያጭ ለማስወገድ ጨረታ አውጥቶ ጨረታውን መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡15 ሰዓት በአገልግሎቱ አዳራሽ መክፈቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት የጨረታ ሰነድ ግምገማ ተጠናቆ የአሸናፊ ተጫራቾች ውጤት በአገልግሎቱ ቦርድ ላይ ይፋ መደረጉን  ከመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

                        በሚቀጥለው  

አገልግሎቱ የሞተር ሳይክል ግዥ ለመፈፀም አለም አቀፍ ግልፅ የጨረታ ማስታወቂያ አወጣ፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ለኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ እና ለገቢዎች ሚኒስቴር አገልግሎት የሚውሉ የተሽከርካሪ (ሞተር ሳይክል) ግዥ ለመፈፀም አለም አቀፍ ግልፅ የጨረታ ማስታወቂያ ያወጣ ሲሆን ጨረታውም ጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡15 ሰዓት ላይ በአገልግሎቱ አዳራሽ ይከፈታል፡፡ በተጨማሪም የጨረታ ማስታወቂያው በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ(www.ppa.gov.et) እና በአገልግሎቱ ድረ-ገጽ (pppds.gov.et) ላይ እንዲጫን ተደርጓል፡፡

 

                       

 

 

የተለያዩ ሞተር ሳይክሎች 

 በአገልግሎቱ የማስፈጸም አቅምን የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን ለመስጠት መታቀዱ ተገለጸ 

ለአገልግሎቱ አመራሮች እና ሰራተኞች የአቅም ክፍተትን መሰረት ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን መስጠት፣የልምድ ልዉዉጥ እና የእርስ በእርስ መማማርን የማጠናከር የክህሎት ክፍተቱን መሙላት እንዲሁም በዘለቄታ የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት የማስፈፀም አቅም ማሳደግ በ2014 በጀት ዓመት ቅድሚያ የሚሰጠዉ ተግባር መሆኑ ተገለፀ፡፡ 

     አገልግሎቱ ከሚወገዱ ንብረቶች የሚገኝ ገቢን ለማሳደግ ማቀዱን ገለፀ

በተያዘው በጀት ዓመት ከጨረታ ሰነድ ሽያጭ ብር 387 ሺህ፤50 ባለበጀት መ/ቤቶችና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 200 ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በጨረታ በመሸጥ ብር 60 ሚሊዮን ገቢ እና የ40 ባለበጀት መ/ቤቶችና መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 900 ሎት ያገለገሉ ንብረቶች በጨረታ በመሸጥ ብር 13 ሚሊዮን በአጠቃላይ 73 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት ለመንግስት ግምጃ ቤት ፈሰስ ለማድረግ በእቅድ መያዙን ከመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

አገልግሎቱ በ2014 በጀት ዓመት የማዕቀፍ፣ የስትራቴጂክ እና ሌሎች ግዥዎችን ሊፈጸም ነው፡፡

አገልግሎቱ በ2013 በጀት ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ 7 ግዥዎችን ማጠናቀቅ፤ለፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች እና ለ18 ዩኒቨርስቲዎች የቢሮ ፈርኒቸር ግዥ፣ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ከ27-30 ሰው መጫን የሚችሉ 15 ኮስተር ባሶች ከአስመጭው ቀጥታ ግዥ፣ለገቢዎች ሚኒስቴር 40 ፒክአፕ ደብል ጋቢና ከዱባይ ሃገር በዋጋ ማቅረቢያ ግዥ፣ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አገልግሎት የሚውል የAutomated Biometric Identification System እና Crime Scene Investigation Vehicle and Equipment ግዥ፣ለፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶችና ለመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከ2014-2016 በጀት ዓመት አገልግሎት የሚውል የጋራ መጠቀሚያ እቃዎች በ6 ሎት ግዥ መፈጸም፣አገራዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን እቃዎች እና አገልግሎቶች ተጠቃሚ መ/ቤቶች በሚያቀርቡት ፍላጎት ላይ በመመስረት የስንዴ፣552 የተለያዩ አይነት ተሸከርካሪዎች እና 60 ሞተር ሳይክሎችን እንዲሁም የላብራቶሪ እቃዎችን እና የማጣቀሻ መፅሐፍትን ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ ግዥ በመፈጸም የመንግስትን ሃብት ከብክነት ለማዳን በ2014 በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዘ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጥራታቸውን የጠበቁ የዕቃዎችን ግዥ ለመፈጸም የቴክኒክና ጥራት ማረጋገጥ ስራዎች እንደሚሰሩ ተገለጸ

በ2014-2016 በጀት ዓመት ለፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች እና ለመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሚዉሉ የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎች ላይ በውል አስተዳደር ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን በመፈተሽ ስፔሲፊኬሽን ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም አዲስ ስፔሲፊኬሽን የማዘጋጀት ስራዎች በ2014 በጀት ዓመት በትኩረት የሚሰሩ ስራዎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ውጤታማ የውል አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ክትትል እንደሚደረግ ተገለጸ

አቅራቢ ድርጅቶች በውሉ መሰረት ዕቃዎችን በጊዜ፣ በጥራት እና በሚፈለገው መጠን እያቀረቡ መሆኑን እና ተጠቃሚ ተቋማት በውሉ መሰረት ዕቃዎችን በጊዜ፣ በጥራት እና በሚፈለገው መጠን እያገኙ መሆኑን በመከታተል እንዲሁም የዕቃዎች ርክክብ ሲፈጸም የመስክ ጉብኝት በማድረግ የድህረ አቅርቦት ፍተሻ (Post Delivery Inspection) በማከናወን በተያዘው በጀት ዓመት ውጤታማ የውል አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ክትትል እንደሚያደረግ የውል አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በእቅዱ አመላክቷል:: 

 

የአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞች በ2013 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀምና በ2014 በጀት ዓመት እቅድ ዙሪያ ውይይት አካሄዱ:: 

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች በ2013 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና በ2014 በጀት ዓመት እቅድ ዙሪያ በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄዱ:: በዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተፈራ ሰይፉ የ2013 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱም  በበጀት ዓመቱ ለፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች እና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሚዉሉ የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎችን እና አገራዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ግዥዎች በመፈጸም በ10 ቢሊየን ብር ለአሸናፊ አቅራቢ ድርጅቶች የአሸናፊነት ደብዳቤ እንደተሰጠና በንብረት ማስወገድ በኩልም በበጀት ዓመቱ የ74 መ/ቤቶች 144 ተሽከርካሪዎች እና የ40 መ/ቤቶች 628 ሎት ያገለገሉ ንብረቶችንና የተሸከርካሪ መለዋወጫዎችን እንዲሁም፣አልሙኒየምና ስቲል ቁርጥራጭ ብረታብረቶችን በሽያጭ  በማስወገድ በድምሩ 63.7 ሚሊዮን ብር ገቢ በማስገኘት ለመንግስት ግምጃ ቤት ፈሰስ መድረጉን ገልፀዋል::

 

                   

                          

         የ2013 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት  

የዕቅድ ዝግጅት ባለሙያው አክለውም በሌሎች የአገልግሎቱ ግቦች ዙሪያ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን እና በበጀት ዓመቱም ያጋጠሙ ችግሮችንና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን አብራርተዋል::                       

የአገልግሎቱን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ያቀረቡት ደግሞ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ረድኤት ተክሉ ሲሆኑ የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ከ2013-2017 ዓ.ም የተዘጋጀውን የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ መነሻ ያደረገ፣በአገልግሎቱ የማኔጅመንት አባላት እና በቦርድ አባላት ሰፊ ውይይት ተደርጎበትና በርካታ ግብዓቶች ተካተውበት የተዘጋጀ፣ የሚለካና ማን ምን እንደሚሰራ የሚያሳይ እቅድ መሆኑን ገልጸዋል::

ወ/ሮ ረድኤት አክለውም እቅዱ በሶስት ምዕራፍ እንደተከፈለና በዝግጅት፣በትግበራና በማጠቃለያ ምዕራፍ ስር የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል::

 

                

የ2014 በጀት ዓመት እቅድ በቀረበበት ወቅት            

በመቀጠል በቀረበው የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና እቅድ ዙሪያ ከሰራተኞች የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣የአገልግሎቱን እቅድና አፈጻጸም በዚህ መልኩ ወጣ ብሎ መገምገም ሰራተኛውን ለስራ የሚያነሳሳ እና ጥሩ ጅምር በመሆኑ መቀጠል እንዳለበት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ስራዎች ለምሳሌ E-GP,IFMIS, Automation ስራዎች በሪፖርቱ ውስጥ እንዳልተካተቱ፣በቢሮ ጥበት ምክንያት ያለው የሰው ኃይል በመዋቅሩ ከተፈቀደው ከ50 ፐርሰንት በታች በመሆኑ ስራዎችን በሙሉ አቅም ለመስራት እንዳልተቻለ፣ አነስተኛ ደመወዝ ያላቸው ሰራተኞች በኑሮ በጣም እየተፈተኑ ስለሆነ አገልግሎቱ የደመወዝ ጭማሪ ላይ ምን አስቧል? የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባችው ግዥዎች ለምሳሌ የደንብ ልብስ ግዥ እየተሳካ ስላልሆነ ከእቅድ ቢወጣ የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን የቢሮ ጥበት የአገልግሎቱ ዋናው ችግር በመሆኑ ወደ ፊት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት እንደሆነ፣ የሰው ኃይል ሙሌትን በሚመለከት በሂደት ላይ ያሉ ቅጥሮች በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቁ፣ የደመወዝ ጭማሪ እንደ ሀገር የሚስተካከለው በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኩል እንጅ በአገልግሎቱ ደረጃ ማሻሻያ እንደማይደረግ፣የመልካም አስተዳደር ያለባቸው ግዥዎች ከእቅድ ቢወጡ የተባለው ትክክል እንዳልሆነና ትኩረት ተሰጥቶት ስራው መሰራት እንዳለበት ተገልጿል::

             በእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱና በእቅዱ ላይ ውይይት ሲካሄድ

ከ2013 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና ከ2014 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት በተጨማሪ ተቋማዊ ባህል ምንድነው? ጥራት ያለው ተቋማዊ ባህል በምን ይገለፃል፣መልካም ያልሆነ ተቋማዊ ባህል የሚገለጽባቸው ሁኔታዎች በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ በአገልግሎቱ የሰው ሀብት ልማትና አተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ዘሪሁን ስለሽ ለአገልግሎቱ ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡  

 

  በተቋማዊ ባህል ምንነትና መገለጫዎች ዙሪያ ስልጠና ሲሰጥ

በመጨረሻም የአገልግሎቱ  ዋና  ዳይሬክተር  ወ/ሮ ጽዋዬ  ሙሉነህና  የመንግስት ንብረት አስተዳደር/ገበያ ጥናት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢቲሳ ደሜ
ውይይቱን  አስመልክተው  መልዕክት   ያስተላለፉ  ሲሆን የተቋሙን ራዕይ ለማሳካት ሁላችንም ጠንክረን መስራት እንዳለብን በማሳሰብ መጪው  አዲስ ዓመት የሰላም፣የጤናና የስኬት ዓመት እንዲሆን ለሰራተኞች መልካም  ምኞታቸውን  በመግለጽ ውይይቱን አጠናቀዋል:: 

 

 

የአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞችየአረንጓዴ አሻራ” የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አካሄዱ፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ባለፉት ዓመታት በአገር ዓቀፍ ደረጃ በተከናወነው የአረንጓዴ ልማት አሻራቸውን ማሳረፍ መቻላቸው የሚታወስ ነው፡፡ ስለሆነም በዘንድሮው ዓመትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሶስተኛ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው የአረንጓዴ ልማት አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የመ/ቤታችን አመራሮችና ሠራተኞች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ የድርሻቸውን አሻራ ለማስቀመጥ መሳተፍ እንዳለባቸው በአገልግሎቱ የግዥና ውል አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አበባ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡ 

                                  

በዚህም መሰረት የአገልግሎቱ አመራሮች እና ሠራተኞች ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም በእንጦጦ ፓርክ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄደዋል፡፡ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም 5ሺ አገር በቀል የዛፍ ችግኞችን የመትከል ስራ ተከናውኗል፡፡

 

 

 

                 የአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞች በእንጦጦ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተካላ ፕሮግራም ሲያካሄዱ

                                  

በመጨረሻም በአገልግሎቱ የመንግስት ንብረት አስተዳደር/የገበያ ጥናት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢቲሳ ደሜ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ ልማት አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ አሻራቸውን ለማስቀመጥ ለተሳተፉ የአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞች ምስጋና በማቅረብ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብም አስፈላጊ በመሆኑ በቀጣይ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡  

 

  የቢሮ መገልገያ ዕቃዎችን ግዥ ለመፈፀም በ54.1 ሚሊየን ብር አዋርድ ተሰጠ

 

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በማዕቀፍ ስምምነት ከ2013-2015 በጀት ዓመት የሚቆይ ለ18 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሚውል ሎት አንድ የተለያዩ የቢሮ መገልገያ ዕቃዎችን ግዥ ለመፈፀም ባወጣው ጨረታ ላይ ከተወዳደሩት ተጫራቾች አሸናፊ ለሆነው ተጫራች GM Furniture S.C 54,145,931.24 ብር አዋርድ ሰጠ፡፡   

በተቀናጀ የሰው ሀብት ሥራ አመራር መረጃ ሥርፀት (ICSMIS) አተገባበር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

ለመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች የተቀናጀ የሰው ሀብት ሥራ አመራር መረጃ ሥርፀትን (ICSMIS)ን ተግባራዊ ለማድረግ በአተገባበሩ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ ስልጠናው ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመጡ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ዋና ዓላማውም በሰው ሀብት አስተዳደር በማኑዋል የሚከናወኑ ስራዎች ለምሳሌ  የዋስትና ጥያቄ፣ የፈቃድ፣የጡረታ፣ በቅጥር ፣በደረጃ እድገትና በዝውውር ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎች እና ሌሎችንም ስራዎች ወደ ሲስተም በማስገባት በኦንላይን ስራዎችን ለመስራትና በማኑዋል ሲሰራ የሚባክነውን ወጪና ጊዜ ለመቆጠብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡   

 

          

 በተቀናጀ የሰው ሀብት ሥራ አመራር መረጃ ሥርፀት (ICSMIS)

            አተገባበር ዙሪያ  ስልጠና ሲሰጥ

 

                       በሚቀጥለው   

   በሽያጭ የሚወገዱ ያገለገሉ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች የጨረታ ሰነድ እየተሸጠ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የ14 መ/ቤቶችን 25 ያገለገሉ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችን በሽያጭ ለማስወገድ ጨረታው ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ወጥቶ የጨረታ ሰነድ እየተሸጠ ሲሆን ጨረታውም መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡15 ሰዓት በአገልግሎቱ አዳራሽ እንደሚከፈት ከመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቀንድ ከብቶችን በግልፅ ጨረታ ለመሸጥ የጨረታ ሰነድ ግምገማ

እየተካሄደ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ንብረት የሆኑ የቀንድ ከብቶችን በግልፅ ጨረታ ለመሸጥ ጨረታውን ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም የከፈተ ሲሆን የጨረታ ሰነድ እየተገመገመ መሆኑን ከመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

 በሽያጭ የሚወገዱ ያገለገሉ ልዩ ልዩ ንብረቶች የጨረታ ማስታወቂያ መውጣቱ ተገለፀ፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የ5 መ/ቤቶችን ያገለገሉ ልዩ ልዩ ንብረቶች  በሽያጭ ለማስወገድ ጨረታው ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የወጣ ሲሆን   በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲና በአገልግሎቱ ድረ-ገጽ ላይም እንዲጫን ተደርጓል፡፡ ጨረታውም መስከረም 10 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡15 ሰዓት ላይ በአገልግሎቱ አዳራሽ እንደሚከፈት ከመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡